Monday, December 22, 2014

ቶም እና ጄሪ

By Daniel Kibret

«ቶም እና ጄሪ» ፊልም ዊልያም ሐና እና ዮሴፍ ባርባራ በተባሉ ባለሞያዎች ለሜትሮ ጎልድዊን ካምፓኒ የተሠራ ተከታታይ የካርቱን ፊልም ነው፡፡ የቤት ውስጥ ድመት በሆነው በቶም እና በተንኮለኛዋ አይጥ በጄሪ መካከል በማያቋርጥ ቅንቃኔ እና ጠላትነት እየተቀጣጠለ የሚሄደው ይሄ ፊልም፣ አስገራሚም አስቂኝም ነው፡፡ 

በ1940 እኤአ የተጀመረው ቶም እና ጄሪ፣የአኒሜሽኑ ኩባንያ እስከ ተዘጋበት እስከ 1957 እኤአ ብቻ 114 ያህል ተከታታይ ፊልሞችን በሐና እና በባርባራ ደራሲነት እና አዘጋጅነት አቅርቧል፡፡

በ1960 እኤአ በአዲስ መልክ ፊልሙ እንደ ገና መዘጋጀት እና መታየት ጀመረ፡፡ ዛሬ በታይም ዋርነር ካምፓኒ ባለቤትነት እና በዋርነር ብሮስ አከፋፋይነት የተያዘው የቶም እና ጄሪ የካርቱን ፊልም 162 ተከታታይ ፊልሞችን ያጠቃልላል፡፡

ቶም እና ጄሪ አብረው በአንድ ሰው ቤት ውስጥ የሚኖሩ ነገር ግን መቼም ቢሆን ተስማምተው የማያውቁ ፍጡራን ናቸው፡፡ አልፎ አልፎ በጥቅም ምክንያት ሲስማሙ እንኳን በአከፋፈሉ ምክንያት ለመጣላት ጊዜ አይወስድባቸውም፡፡ ሁለቱንም የሚቃረን ነገር ከመጣ ግንባር የሚፈጥሩት ቶም እና ጄሪ፣ የጋራ ጠላታቸውን ለየራሳቸው ምክንያት ሲሉ ካጠቁ በኋላ እንደገና እርስ በርሳቸው መጣላት ይቀጥላሉ፡፡


ይህ፣ መቼም የማያባራ የቶም እና የጄሪ የቅንቃኔ እና የጠላትነት ፊልም፣ በባለቤቶቹ ዘንድ የታወቁ 162 ተከታታይ ፊልሞች አሉት ቢባልም ጠቅላላ የፊልሞቹ ብዛት ግን ከዚህ ሳይበልጥ አይቀርም፡፡ ለምሳሌ 163ኛው ፊልም የሚዘጋጀውም፣ የሚሠራውም፣ የሚቀርበውም እኛው ሀገር ነው፡፡ ፊልሙን የደረሱትም፣ የሚያዘጋጁትም፣ የሚተውኑትም የ1960ዎቹ የኢትዮጵያ ትውልዶች ናቸው፡


ቶም እና ጄሪ በአንድ ሰው ቤት የሚኖሩ ባላንጣዎች ናቸው፡፡ የ1960ዎቹ የሀገራችን ትውልዶችም በአንድ ወቅት የተነሡ የአንዲት ሀገር ልጆች ናቸው፡፡ የተነሡበት ዓላማም ተመሳሳይ ነው፡፡ እነርሱ በሚያስቡት መንገድ ብቻ ሀገሪቱን ማሳደግ፡፡ የርእዮተ ዓላማቸውም ቤቱ ተመሳሳይ ነው፡፡ ያም የብዕር ስሙ ይለያይ እንጂ ከኮሚኒስታዊ አስተሳሰብ አይዘልም፡፡ ፀር፣ትግል እና ግንባር ይወዳሉ፡፡

ዛሬ በሀገሪቱ የወዲህም ሆነ የወዲያ ጎራ፣በድጋፍም ሆነ በተቃውሞ፣ በሀገር ውስጥም ሆነ በዲያስጶራ የሚገኙ፤ የፖለቲካው እና የቤተ እምነቱን መዘውር የሚዘውሩ አካላት በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ከ1960 እስከ 1970 ዓም ባለው ጊዜ ውስጥ የተነሡ፤ በዚያ ዘመን በነበሩ የፖለቲካ አስተሳሰቦች የተማረኩ፣ የዚያን ዘመን የፖለቲካ አመለካከቶችን ሲያቀነቅኑ የነበሩ ናቸው፡፡

ወይ ኢሕአፓ፣ወይ ኢዲዩ፣ወይ መኢሶን፣ወይ ኢሠፓ፣ወይ ኢጭአት፣ወይ የተማሪዎች ንቅናቄ፣ ወይ የሠራተኞች ንቅናቄ፣የላብ አደር ፓርቲ፣ኢማሌድኅ፣ሰደድ ወዘተ ውስጥ ገብተው ሲቆራቆሱ እና ሲተረማመሱ፤ አንዱ ሌላኛውን ለማጥቃት ቀይ ሽብር እና ነጭ ሽብር ሲያካሂዱ፣ አብዮታዊ ርምጃ ሲወስዱ እና ተቀናቃኞቻቸውን አብዮታዊ ምት ሲመቱ የነበሩ ናቸው፡፡

በውይይት ክበብ፣ በማሌ ጥናት፣በስብሰባ አካሄድ፣በፓርቲ አመሠራረት፣ጭቁኑን ሕዝብ በማታገል መርሕ አልስማማ ብለው ወይ ተጣልተዋል፣ ወይ ተኳርፈዋል፣ ወይ ተለያይ ተዋል፣ወይ ተፈላልገዋል፣ወይ ቂም ተያይዘዋል፣ ወይ ጥርስ ተነካክሰዋል፡፡ ስለዚህም እንደ ቶም እና ጄሪ አንዱ ሌላውን በጠላትነት እያየ ከመቀናቀን የተሻለ ሌላ ፊልም ለመሥራት ያዳግታቸዋል፡፡

«የምጠላው ወይም የምቃወመው አታሳጣኝ» ብለው የተሳሉ ይመስል ያለ ጠላት መኖር አይችሉም፡፡ አንዳንድ ጊዜ ቶም፣ ድሮ ጄሪ ያደረገችበትን ተንኮል ፊልሙን መልሶ እያየ ይበሳጫል፡፡ ከመበሳጨትም አልፎ ለመበቀል እርሷን ፍለጋ ይሄዳል፡፡ እነዚህም ከስድሳ ስድስት እስከ ሰባ ዓም የተቀረጸውን የደም መፋሰስ ፊልም ደጋግመው እያዩ አንዱ ሌላውን በኋላ ታሪኩ ምክንያት ለማጥቃት ይፈላለጋሉ፡፡

162 ፊልሞች ሲሠሩ ቶምም ሆነ ጄሪ አሁንም የፊልሙ ዋነኛ ተዋናዮች ናቸው፡፡ አልተ ቀየሩም፡፡ ከ1940 እስከ 2009 ፊልሙን የሚሠሩት ቶም እና ጄሪ ናቸው፡፡ አልተለወጡም፡፡ በ1960ዎቹ የነበሩት ልጆች ያዩት የቶም እና ጄሪ ፊልም ዛሬም በሃያኛው መቶ ክፍለ ዘመን ያሉ ልጆችም ያዩታል፡፡ በኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክም ፊልሙ እንደ ቶም እና ጄሪ አልተቀየረም፡፡ ያው ነው፡፡ በ1960ዎቹ የነበሩት የሀገራችን የፖለቲካ ቶም እና ጄሪዎች ዛሬም አሉ፡፡ የፖለቲካው ፊልም ዋነኛ ተዋናዮች እነርሱው ናቸው፡፡ አሁንም ሀገሪቱ ከ1960ው ትውልድ ተጽዕኖ መላቀቅ አልቻለችም፡፡ መቼ ይሆን ከስድሳዎቹ ወጥተን ወደ ሰባዎቹ፣ ወደ ሰማንያዎቹ፣ ወደ ዘጠናዎቹ እና ወደ ሁለተኛው ሺ የምንገባው? አሁንምኮ በየፖለቲካው መድረክ የምናያቸው ትክለ ሰብእናዎች የዛሬ ሠላሳ ዓመት የነበሩትን ነው፡፡

አዲሱ ትውልድም የቶም እና ጄሪ ፊልምን ስለለመደ በተመሠረቱት ነገሮች ሁሉ እነዚህን አካላት ካላካተተ፤ ወይንም እነዚህ አካላት ቡራኬ ካልሰጡት በቀር ይሳካል ብሎ ማመን ያቆመ ይመስለኛል፡፡

ገበየሁ ቢሞት ተተካ ባልቻ

መድፍ አገላባጭ ብቻ ለብቻ

ተብሎ በተዘፈነባት ሀገር፣ዛሬ ዛሬ ገበየሁም አይሞት ባልቻም አይተካ፡፡

ቶም እና ጄሪ ቦታ ይቀያየራሉ እንጂ ስልትም መንገድም አይቀይሩም፡፡ ውጭ የነበረው ቶም ቤት ሲገባ ጄሪ ከቤት ትባረራለች፣ያለበለዚያም ጄሪ ቤት ገብታ ቶም ይባረራል፡፡ ዛሬ የአንድ ፓርቲ ሊቀመንበር የነበረው ነገ የሌላ ይሆናል፤ የአንድ ፓርቲ ልሳን ሲያዘጋጅ የነበረው ምንም ዓይነት የአመለካከት ለውጥ ሳያደርግ ሌላው ጋር ይቀላቀላል፡፡ ደንበኛ ጥናት አድርገን ብንፈትሽ ዛሬ የቆሙለትን ዓላማ ደግመው ደጋግመው ሲቃወሙት የነበሩ አስገራሚ ቶም እና ጄሪዎችን በሀገራችን ታሪክ እናገኝ ነበር፡፡ እነዚህ ሰዎች የፖለቲካ አመለካከታቸው የሚወሰነው እንደሚያምኑበት ነገር ሳይሆን እንደ ሚገቡበት ድርጅት እና እንደሚሠጣቸው ሥልጣን ነው፡፡

ቶም እና ጄሪን የሚያስማሟቸው ሁለት ነገሮች ብቻ ናቸው፡፡ የመጀመርያው ጥቅም ሲሆን ሁለተኛው የጠላት መኖር ነው፡፡ በኛም የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ይሄው ፊልም እንደ ቀጠለ ነው፡፡ ቶሞች እና ጄሪዎች አንድ የሚሆኑት ጥቅም እስከተገኘ ድረስ ብቻ ነው፡፡ ጥቅም ከተገኘ በርእዮተ ዓለሞቻቸው ላይ እንኳን የረባ ውይይት ሳያደርጉ፤ የቱጋ የአቋም ለውጥ እንዳደረጉ በሚገባ ሳይረዱም ሳያስረዱም በቅጽበት ይቀናጃሉ፣ ይተባበራሉ፤ ይዋሐዳሉ፣ግንባር ይመሠርታሉ፡፡ አከፋፈል ላይ ሲለያዩ ደግሞ የተባበሩ ቀርቶ የተጎራበቱ መሆናቸውን እስክንጠራጠር ድረስ ይናከሳሉ፡፡

ቶም እና ጄሪ ጠላት መጣብን ብለው ሲያስቡ አንድ ሆነው ያባርሩትና ከጠላታቸው በባሰ መልኩ እርስ በርሳቸው ይባላሉ፡፡ የሀገራችን ቶሞች እና ጄሪዎችም ሊያጠፋን ነው ብለው የሚያስቡት ጠላት ሲያጋጥማቸው አብረው ይሰበሰባሉ፣ይወስናሉ፣መግለጫ ያወጣሉ፣ ይሰለፋሉ፡፡ በኋላ ግን ጠላት ነው ብለው ከሚያስቡት አካል በባሰ ሁኔታ እርስ በርሳቸው መበላላት ይቀጥላሉ፡፡

ለቶም እንደ ጄሪ፣ለጄሪም እንደ ቶም የሚቀርባቸው የለም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ለቶም እንደ ጄሪ፣ ለጄሪም እንደ ቶም የሚጎዳቸው የለም፡፡ የኛም ፖለቲከኞች ይህንኑ ፊልም በመሥራት ላይ ናቸው፡፡ 163ኛውን ክፍል፡፡

ባለፈው ጊዜ የዘመን አቆጣጠራችንን ብቻ ተመልክተን ሁለተኛውን ሺ አከበርነው እንጂ የፖለቲካ አቆጣጠራችን ብናየው ኖሮ ወደ ሁለተኛው ሺ ለመግባት ቢያንስ ገና ሠላሳ ያህል ዓመታት በቀሩን ነበር፡፡ አሁንም ተቃውሞ እና ጠላትነትን አልለየንም፣ አሁንም ገና ደጋፊነትን እና ምእመንነትን አልለየንም፡፡ ተቃዋሚያችን ምንም ዓይነት በጎ ነገር ቢያስብ ከመቃወም አንመለስም፤ ጠላትነት እንጂ ተቃውሞ አናውቅማ፡፡ የምንደግፈው አካልም ምንም ዓይነት ጥፋት ቢያጠፋ ከማመስገን ወደ ኋላ አንልም፤ ምእመንነት እንጂ ድጋፍ አናውቅማ፡፡ አይቶም እና ጄሪ፡፡

ሰሞኑን እዚህ ኔዘርላንድ በአንዳች ምክንያት የተጣሉ ሁለት ኢትዮጵያውያን ጎራዎችን ለማስታረቅ የተሰየሙ የሀገሬ ሽማግሌ ያሉኝን እዚህ ላይ ብጠቅሰው እንዴት ጥሩ ነው፡፡ አንደኛው ወገን ከሌላው ወገን ጋር ለመታረቅ በቅድመ ሁኔታነት አሥራ አምስት ነጥቦችን ያስቀምጣል፡፡ ሽማግሌዎቹም ይህንኑ ይዘው ወደዚያኛው ጎራ ይሄዱና ጉዳዩን ያቀርባሉ፡፡ እነዚህኞቹም ቡድኖች ከተወያዩ በኋላ አሥራ አምሱንም ነጥቦች በሙሉ እንቀ በላለን ብለው መልስ ይሰጣሉ፡፡ ሽማግሌዎቹም ድካማቸው ፍሬ በማፍራቱ ተደስተው ወደነዚያኞቹ ይሄዱና «እነዚያኞቹ በሃሳባችሁ ሙሉ በሙሉ ተስማምተዋል» ይሏቸዋል፡፡ ሰዎቹ አላመኑም «አሥራ አምስቱንም ነገር ተቀበሉት?» ይላሉ፡፡ «አዎ ሁሉንም ተቀብለዋል»፡፡ «እንዴት አንድ ሁለቱን እንኳን አልተቃወሙም፤ አንዳች ነገር ቢያስቡ ነውና እንዲያውም አንታረቅም» ብለው መልሱን አሉኝ፡፡

እውነታቸውን ነው፡፡ ቶም እና ጄሪአይደሉ፤ አንዳች የሚያጣላ፣ የሚያቆራቁስ፣ ለፓል ቶክ፣ ለዌብ ሳይት እና ለወሬ የሚሆን የጠብ መነሻማ ያስፈልጋቸዋልኮ፡፡ ተስማምተው ከሠሩ ምን ሊውጣቸው ነው? በኋላ በምን ተለያየን ሊሉ ነው፡፡ አይ ቶም እና ጄሪ፡፡

ኢትዮጵያዊውን የቶም እና ጄሪ ፊልም ከቁጥር አንድ ጀምራችሁ የምትተውኑ የፖለቲካ ቶም እና ጄሪዎች ጠቅላይ ሚኒስትራችን እንዳሉት በቃን ብትሉ ምናለ? ቢያንስ ለአፋችሁ ያህል፡፡ ሀገሪቱ 1960ዎቹን ለቅቃ ወደ ሃያኛው ክፍለ ዘመን ትገባ ዘንድ ብትረዷት ምናለ፤ በአንድ ወቅት በአንድም በሌላም መልኩ የቶም እና ጄሪን ፊልም የጀመራችሁ ተዋንያን፣ እባካችሁ ሌላ ፊልም እንይበት፡፡ የመነካከስ እና የመበላላት፣ የማያቋርጥ ቅንቃኔ እና ጠላትነት ተከታታይ ፊልም ሰልችቶናል፡፡

ሮተርዳም፣ኔዘር ላንድ

No comments:

Post a Comment