ጲላጦስ Wednesday, March 31, 2010
By DanielKibret.com
ሚያዝያ
14 ቀን 2000 ዓ.ም በኢትዮùያ አየር መንገድ የበረራ ቁጥር ET 603 ከዱባይ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ላይ
ነበርኩ፡፡ ሻርጅያ በተባለው ከተማ አንድ ኢትዮ ጵያዊ የጠየቀኝን ጥያቄ አወጣለሁ፣ አወርዳለሁ፡፡ ወቅቱ በኢትዮጵያ
ክርስቲያኖች ዘንድ ‹ሰሙነ ሕማማት› የሚባለው ነው፡፡ ሚያዝያ 17 ቀን ስቅለት ከሁለት ቀናት በኋላ ደግሞ
የትንሣኤ በዓል ይከበራል፡፡
ያ ኢትዮጵያዊ ወዳጄ፡- ‹‹መስፍኑ ጲላጦስ
ክርስቶስን ለምን አሳልፎ ሰጠው?›› የሚል ጥያቄ ነበር ያነሣልኝ፡፡ ለጊዜው ይኾናል ያልኹትን ማብራሪያ ሰጠኹት፡፡
በኋላ ግን እኔው ራሴ በነገሩ ማሰላሰሌን ቀጠልኹ፡፡
ጴንጤናዊው
ጲላጦስ ክርስቶስ በተሰቀለበት ጊዜ (በ34 ዓ.ም) በኢየሩሳሌም የሮምን ንጉሥ በመወከል የይሁዳ መስፍን ነበር፡፡
ክርስቶስ በፊቱ ተከስሶ የቀረበውም ከዚህ ሥልጣኑ የተነሣ ነበር፡፡ በዘመኑ ይደረግ እንደ ነበረው ተከሳሹን አስቀርቦ
ጠየቀ፡፡ እር ሱን ያስረዳሉ የተባሉ የከሣሽ ምስክሮችንም ጠየቀ፡፡ ነገር ግን ኢየሱስ ክርስቶስን ‹‹ወንጀለኛ››
ሊያስደርግ የሚችል ምንም ነገር ዐጣ፡፡ ሚስቱም በሕልሟ ያየችውን ነገር በመግለጥ በርቱዕ መንገድ ብቻ ፍርድ
እንዲሰጥ ነገረችው፡፡
እነዚህ
ሁሉ ተደማምረው መስፍኑ ጲላጦስ ክርስቶስን፡- ‹‹ለሞት የሚያበቃው ቀርቶ የሚያሳስረው ጥፋት አላገኘሁበትም›› ሲል
ደመደመ፡፡ አይሁድ ይህን ሲሰሙ ‹‹ይህን ካደረግኽ የቄሣር ወዳጅ አይደለህም›› የሚል ፖለቲካዊ ተቃውሞ በከረረ
ሁኔታ መሰንዘር ጀመሩ፡፡ ጲላጦስ ነገሩን ለማብረድ በማሰብ ‹‹ኢየሱስ ክርስቶስን ገርፌ ልስቀልላችሁ›› የሚል
አማራጭ ሐሳብ አቀረበ፡፡ ከሳሾቹ አይሁድ ግን ‹‹ሞቶ ካላየነው አንተ የቄሣር ወዳጅ አይደለህም›› ብለው ነገሩን
አጠነከሩት፡፡ በመጨረሻም መስፍኑ ጲላጦስ ተሸነፈ እና ይሙት በቃ ፈረደ፡፡
የተከሰሰው
እና በፍርድ አደባባይ የቆመው ክርስቶስ ምንም ጥፋት እንዳላጠፋ ዳኛው ዐውቋል፡፡ ማወቅ ብቻም ሳይኾን በአንደበቱ
መስክሯል፡፡ ሕጉም ንጹሕ የኾነ ሰው ከተከሰሰበት ነገር ነጻ እንዲኾን እና እንዲሰናበት ያዝዛል፡፡ ታዲያ ጲላጦስ
ይህን ሁሉ እያወቀ ለምን የተዛባ ፍርድ ፈረደ?
አንድን
ነገር ማወቅ፣ በጉዳዩም ማመን እና ላመኑበት እውነት እስከ መጨረሻው በጽንዐት መቆም የተለያዩ ነገሮች ናቸው፡፡
ጲላጦስ የዕውቀት ችግር አልነበረበትም፡፡ በዘመኑ በነበረው የፍርድ አሰጣጥ ሥነ ሥርዐት መሠረት የከሳሾቹን
ምስክሮችም ኾነ ተከሳሹን በፊቱ አቁሞ ጠይቋል፡፡ በዚህም ክርስቶስ ምንም ወንጀል የሌለበት መኾኑን ዐውቋል፡፡ ነጻ
መኾን እንዳለበትም አምኗል፡፡ ይህን ዕውቀቱን እና እምነቱን በተግባር እንዳያውል ግን አንድ ነገር ከለከለው -
የሚያጣው ጥቅም፡፡
ክርስቶስ
የተከሰሰበት አንዱ ወንጀል ‹‹ራሱን ከቄሣር ጋር በማስተካከል ‹ንጉሥ ነኝ› ይላል›› የሚለው ነው፡፡ በመኾኑም
ክርስቶስን ነጻ ቢለቀው ‹‹ከቄሣር ሌላ ንጉሥ አለ ብሎ ያምናል›› ተብሎ ሊወነጀል፣ በኋላም ሥልጣኑን ሊያጣ ነው፡፡
ጲላጣስ እውነ ትን ተቀብሎ፣ ለእውነት መሥዋዕትነት ከፍሎ ሥልጣኑን ከሚያጣ እውነትን ሠውቶ በሥልጣን መቆየትን
መረጠ፡፡ ያመነው ነገር፣ የተናገረው ነገር እና የፈረደው ፍርድ ተለያየ፡፡
አንዳንድ
ሰዎች የሚናገሩት፣ የሚያምኑበት፣ በየመድረኩ የሚደሰኩሩት፣ አጠናን ብለው የሚተነትኑት፣ ከልብ ጓደኞቻቸው ጋር
ሲያወጉ የሚዘረዝሩት፣ ‹‹ቢኾን መልካም ነው›› የሚሉት እና በቦታው ላይ ኾነው የሚፈጽሙት የሚለያየው ለእውነት
መቆም የሚያስከፍለው ዋጋ ስላለ ነው፡፡
አንድ
ዳኛ የሚተቸው፣ የሚተነትነው፣ በኅሊናው የሚያምንበት እና በልቡ የሚያመላልሰው ከሚሰጠው ፍርድ ጋር ከተጋጨ፣ አንድ
ባለሥልጣን እውነት ነው ብሎ የተቀበለው እና ትክክል ነው ብሎ የወሰነው ከተለያየ፣ አንድ ባለሞያ የጥናቱ ውጤት
እና እርሱ ለአለቃው ያቀረበው ውጤት ከተቃረነ እንዳያጡት የሚፈሩት ጥቅም አለ ማለት ነው፡፡
በስብሰባ
ተቀምጠው አለቆቻቸውን ወይም የሚመጣውን መከራ ፈርተው አንዳች ነገር የሚወስኑ ነገር ግን በልቡናቸው የተቀበሉት
እውነት ከወሰኑት ጋር የሚጋጭባቸው ሰዎች ይህን በሽታ የሚያሥታግሱት ‹‹ምን ይደረግ ብለህ ነው፤ በግድ፣ ሳናም
ንበት፣ አስፈራርተው፣ ሐሳባችንን ሳይቀበሉ ቀርተው . . .የማይኾን ነገር ወሰኑ›› እያሉ ለሚቀርባቸው ሰው
በማውራት ነው፡፡ የውስጡን ግጭት በወሬ ነው የሚያስተነፍሱት፡፡
ከወዳጆቻቸው
ጋር ሲቀመጡ የተቹትን፣ የነቀፉትን እና የተቃወሙትን ነገር በቦታው ሲኾኑ ግን ‹‹የጠሉት ይወርሳል. . . ››
የተባለው ደርሶባቸው እነርሱ የባሱ ኾነው ይገኛሉ፡፡ አንዳንድ ጊዜ በሚያምኑት ነገር እና በሚሰጡት መግለጫ መካከል
ቅራኔ ሲያጋጥማቸው በረዥም ዐረፍተ ነገሮች፣ ኧ. . .ኧ. . .ኧ በሚል የሚታክት የነገር ጉተታ ወይም ደግሞ
‹‹አበረታች ነው፤ አስደናቂ ነው፤ ልዩ ነው፤ ብሩህ ነው›› በሚሉ የማይለኩ ነገሮች ሊያሥታግሱት ይሞክራሉ፡፡
ሁለት
እና ሁለት አራት መኾኑን እያወቁ፣ ጠረጴዛቸው ላይ በሚገኘው ወረቀት ይኽንኑ ሳያስቡት እየሞነጫጨሩ፣ 2 እና 2
‹‹አምስት ነው›› ብለው ለማሳመን ሲሉ የማርስ እና የጁፒተርን ልምድ የሚጠቅሱት ኅሊናቸው እና ንግግራቸው
ሲጋጭባቸው ነው፡፡
‹‹የእንጀራ
ጉዳይ ነው፤ ልጆቼን ላሳድግ ብዬ ነው፤ ‹ከሰው ጋር ሲኖሩ ሞኝ ኾኖ አህያ ሲጭኑ ሦስት ኾኖ› ስለሚባል ነው፤ ክፉ
ቀንን እና ቅዝምዝምን ጎንበስ ብሎ ማሳ ለፍ ስለሚገባ ነው፤ ብቻዬን ለውጥ ላመጣ ስለማልችል ነው . . .››
የሚባሉት ማብራ ሪያዎች ሁሉ ከነመሰሎቻቸው የዚሁ ጲላጦሳዊ ችግር መገለጫዎች ናቸው፡፡
ሰው
በመኖር ብቻ ሳይኾን በመሞትም ያሸንፋል፡፡ ሰዎችን ከእንስሳት ከሚለዩ አቸው ነገሮች አንዱ ሰዎች በሞት ሊገታ
የማይችል አሸናፊነት ሊኖራቸው ስለሚችል ነው፡፡ እነ ማርቲን ሉተር ኪንግ፣ እነ ማኅተመ ጋንዲ፣ እነ አብዲሳ አጋ
ተገድለዋል፤ ነገር ግን አሸንፈዋል፡፡ እነዚህ ሰዎች ለሰማዕትነት እንዲበቁ ያደረጋቸው የሚሠሩት ሥራ ከሚያምኑበት
ነገር ጋር እንዲቃረን ባለመፍቀዳቸው ነው፡፡
የተማረው
እና የሚያምንበት ሌላ ኾኖ ጥቅም ብቻ በሚያስገኝለት ክሊኒክ የሚሠራ፣ ጥቅም ብቻ ባለበት ትምህርት ቤት
የሚያስተምር፣ ጥቅም ብቻ ባለበት የፋይናንስ ሥራ ላይ የተሠማራ፣ ጥቅም ብቻ በሚገኝበት የጋዜጠኝነት መስክ የሚኳትን
ስንቱ ነው !! ውሎ አበል፣ የተሻለ ክፍያ፣ የውጭ ዕድል፣ ሥልጣን፣ የወንበር አበል፣ መኪና፣ የሪሴፕሽን ግብዣ፣
ያማረ ቢሮ እና የተደላደለ ቤት ይቀርብኛል ብሎ የማያምንበትን የሚሠራ ስንቱ !!
ጲላጦስ
ውሳኔውን ወስኖ ክርስቶስ ከተሰቀለ በኋላ በሠራው ሥራ መጸጸት ጀመረ፡፡ የውስጡ እምነት እየገፋ፣ ኅሊናውንም
ዕረፍት እየነሳው መጣ፡፡ ያ ሰዓት ግን ምንም ሊያደርግ የማይችልበት ሰዓት ነበር፡፡ የእርሱ ፍርድ ተፈጻሚ ኾኖ
ኢየሱስ ክርስቶስ ተሰቅሏል፡፡ በታሪክ እንደሚነገረው ጲላጦስ እስከ ዕድሜው ፍጻሜ በዚያ በሠራው ሥራ እንደ ተጸጸተ፣
ኅሊናውም ሰላም ሳያገኝ ነው የኖረው፡፡
ነገር
ካለቀ በኋላ ከመጸጸት እና የኅሊና ሰላም ከማጣት ከሚያምኑት እውነት ጋር መቆም እጅግ የተመረጠ ነው፡፡ ጦርነቱ
ሲያበቃ፣ ፖለቲካው ሲቀየር፣ አስቸጋሪው ዘመን ሲያልፍ፣ የችግሩ ጊዜ ሲጠናቀቅ ‹‹እንዲህ ብዬ ነበር፣ እንዲህ
ማድረግ አልነበረብኝም፤ ያደረግኹት ተገድጄ ነው፤ ተጽዕኖ ነበረብኝ፤ ለታሪክ ምስክርነት ለመትረፍ ብዬ ነው፤በሠራሁት
ሥራ አዝናለሁ፤ ተሰምቶኛል፤ ወዘተ ወዘተ›› ለችግሩ መፍትሔ አይሆኑም፡፡
የሞተው
አይነሣም፤ የደኽየው ሀብት አያገኝም፤ የተነጠቀው አይመለስም፣ ትዳሩን የፈታው አያገባም፤ ያለቀ ዕድሜ አይተካም፤
ያመለጠ ዕድል አይገኝም፡፡ እናም ውስጣዊ ሰላም ይጠፋል፤ ጸጸት እንደ እግር እሳት ይበላል፡፡
በስታድዬሙ
ዙሪያ ተሰብስቦ መተቸት፣ ሐሳብ መስጠት፣ ‹‹ለምን አልገባም›› ብሎ መውቀስ፣ ጎል ሲገባም መጨፈር፣ አሠልጣኝ እና
ተጨዋችን መሳደብ እጅግ በጣም ቀላል ነው፡፡ ከዐሥራ አንዱ ተጨዋቾች እንደ አንዱ ኾኖ ውጤት የሚያመጣ ጨዋታ
መጫወት ግን ከባድ ነው፡፡
የጨዋታ
ጊዜው ሲጠናቀቅ ‹‹ይህ ቢደረግ እንዲህ ይኾን ነበር፤ ያ እንዲህ ቢያደረግ ይገባ ነበር፤ እገሌ ይህን l!ሠራ
አይገባም ነበር፤›› እየተባለ ይተነተናል፡፡ እንዲህ ያለው ነገር ለወደፊቱ ጠቃሚ ልምድ ይገኝበት ይኾናል፡፡ ያን
ጨዋታ ግን አይቀይረውም፤ የገባው ገብቷል፤ የተሳተው ተስቷልና፡፡
እናም
ነገር ካለቀ በኋላ እንዲህ የኾነው እንዲያ ስላልኾነ ነው ከማለት በወቅቱ ማድረግ ያለብንን ነገር ማድረግ ነው፡፡
‹‹አገራችን በባዕድ መያዝ የለባትም›› ብለው ያመኑበትን እምነት በተግባር ለመግለጥ በዐድዋ ዘመቻ መሥዋዕትነት
የከፈሉት ጀግኖ ቻችን ኢትዮጵያን በነጻነት ለማቆየት ችለዋል፡፡ ነገር ግን ‹‹ከጣሊያን የምናገኘው ጥቅም
ይበልጥብናል›› ብለው ባይዘምቱ ኖሮ ታሪክ በተቀየረ ነበር፡፡ ታዲያ ዛሬ እነዚያ ዘማቾች ያልዘመቱበትን ምክንያት
ቢያስረዱን እንኳን የዐድዋን ድል ሊተካው አይችልም፡፡ በክፉ ቀን በጦርነት ሜዳ የተወለዱት ጀግኖች አባቶቻችን ግን
መሥዋዕት ኾነው በሞታቸው ወራሪን አሸነፉ፡፡
ከስብሰባ ሲመጡ፣ ነገር ሲያልቅ፣ ጨዋታው ሲያበቃ፣ መከራው ገሸሽ ሲል ሺሕ ጊዜ ከማውራት ‹‹ጀግና የሚወለደው በጦር ሜዳ ነው›› ብሎ እዚያው ላይ ላመኑበት መሟገት ነው ሞያ ማለት፡፡
ስለ
የሌሊት ወፍ ‹አፈጣጠር› የሰማሁትን እዚህ ላይ ባነሣው መልካም ነው፡፡ በጥንት ጊዜ የሌሊት ወፍ የሚባል ነገር
አልነበረም አሉ፡፡ አንድ ጊዜ ግን ወፎች ተሰብስበው የሚወዳድቀውን ጥራጥሬ አይጦች እየበሉ ጦማችንን ስላሳደሩን
አይጦችን የሚከ ታተል፣ መልኩ አይጥ የሚመስል የወፍ ዘበኛ እንቅጠር ብለው ማስታወቂያ አወጡ፡፡ በዚህ ጊዜ ጉድጓድ
ውስጥ መኖር የመረራት አይጥ ክንፍ አሰፍታ ‹‹ወፍ ነኝ›› ብላ ቀረበች፡፡ ምንም እንኳን ዘመዶቿ ‹‹አይጦች
ጥራጥሬ መብላት የለባቸውም›› የሚሉትን ብትቃወምም ለመኖር ስትል ግን ለዘበኝነቱ ተስማማች፡፡ ጥርሷን አይተው
እንዳያባርሯትም በድንጋይ ሰብራ አረገፈችው፡፡ ለብዙ ዘመን በዘበኝነቱ ጸንታ የገዛ ዘመዶቿ የሆኑትን ወፎች
ስታስበረግግ ኖረች፡፡ እየቆየች ግን ጥርሷ እያደገ፣ ፀጉርዋም እየታወቀ ሄደ፡፡ ለመደበቅ ብትሞክርም አልቻለችም፡፡
ወደ ድሮው ኑሮዋ እንዳትመለስ አይጥነቱን ረስታዋለች፡፡ ያደረገችው ነገር እየጸጸታት ስለ መጣ ከሁሉም ለመራቅ ስትል
በሌሊት ብቻ መንቀሳቀስ ጀመረች ይባላል፡፡ የሌሊት ወፍ አይጥም ወፍም ኾና የኖረችው በዚህ ጠባይዋ ነው ይባላል፡፡
ትናንት
የሠሩት ነገር ‹ጥርሱ እየበቀለ፣ ፀጉሩም ብቅ እያለ› እያስቸገራቸው ስን ቶች ወገኖቼ መከራ እያዩ ነው፡፡
ውስጣቸው አይጥ ኾኖ ላያቸው ወፍ እየኾነ፡፡ እንደ አይጥ እያሰቡ፣ እንደ ወፍ ሊሠሩ እየሞከሩ፣ መጨረሻቸው በጸጸት
ጨለማ ውስጥ መሰወር ይኾናል፡፡
የእስክንድርን
ታሪክ የጻፈው የግብጹ ንጉሥ በጥሊሞስ እንዲህ ይተርክልናል፡፡ በአንድ ትንሽ ጦርነት የእስክንድር ጦር ብዙ ጉዳት
ደርሶበት አሸነፈ፡፡ የዚህ ጦርነት ጉዳት ያንገበገበው አንድ ወታደር ‹‹የአመራር ድክመት ባይኖር ኖሮ ይህን ጦርነት
ለማ ሸነፍ ይህን ሁሉ መሥዋዕትነት መክፈል አያስፈልግም ነበር›› ብሎ በመተቸቱ ተከስሶ እስክንድር ዘንድ ቀረበ፡፡
‹‹ይህ ዓይነቱ ሐሳብ ጦሩን ያዳክማል፤ ጠላትን ያስደስታል፤ መደፋፈር ያመጣል፤ ለሌሎች ክፉ አርኣያ ይኾናልና
ወታደሩም ይቀጣ፣ ሐሳቡም ስሕ ተት መኾኑ ይነገር›› ብለው የጦር ጄኔራሎቹ እስክንድርን ወጥረው ያዙት፡፡
ታላቁ
እስክንድርም ‹‹እንደ ንጉሥነቴ ይህ ሰው ጥፋተኛ ነው፤ የሰነዘረውም አስተ ያየት ስሕተት ነው፤ እንደ እውነቱ
ከኾነ ደግሞ ይህ ሰው ትክክል ነው፤ እኛ ጥፋተኞች ነን፡፡ እኔ ደግሞ እንደ ንጉሥነቴ ሳይኾን እንደ እውነቱ
ፈርጃለሁ›› ብሎ ተናገረ፡፡
No comments:
Post a Comment